የሥራ ባህልን ያዳከመው ባህል

የሥራ ባህልን ያዳከመው ባህል

ሃይማኖት

ሃይማኖት የአንድን ማኅበረሰብ ባህል መቅረጽ ላይ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ሰዎች ከባህል ይልቅ ለሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች የበለጠ ተገዢ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ባህሉም በዚያው ሃይማኖት ልክ የሚቀረጽ ሆኖ ይታያል፡፡ ክርስቲና ብቻ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ከክርስቲያናዊ አስተምህሮዎችና ትውፊቶች ጋር የተያያዙ ባህሎች ይዳብራሉ፡፡ እስልምናም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት በሥራ ባህል ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ወሳኝ ስለሆነ ሥራና ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

ሀ. ምንታዌ አስተሳሰብ

ምንታዌ ወይም የሁለትዮሽ አስተሳሰብ ማለት ሕይወትን መንፈሳዊና ዓለማዊ ብሎ መክፈል ማለት ነው። ሰው ተቀጥሮ የሚሠራውና ገቢ የሚያገኝበት ሥራ ምድራዊ ወይም ዓለማዊ እንደሆነ ያስባል። በተቀራኒው በቤተ ክርስቲያንው ወይም ሃይማኖታዊ ቦታዎች መገኘትን መንፈሳዊ ያደርገዋል። በብዛት ዋጋ የሚሰጠው መንፈሳዊ ተብሎ ለተከፈሉ የሥራ ዓይንቶች ነው። ምድራዊ ነገር እንደማይጠቅም ወይም የመንፈሳዊ ሥራ ተቀናቃኝ አድርጎ ማሰብ ነው።  

ሃይማኖትና ለውጥ

ሌላው በታሪክ  የምንገነዘበው ሃይማኖት ለውጥን የሚገዳደር ኃይል ሆኖ መታየቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የገባው ሃይማኖት ማሰብን፣ መመራመርንና መጠየቅን እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን መሞከር የሚያበረታታ አይመስልም፡፡ በተለይ ‹‹በሃይማኖት ጉዳይ ላይ አትጠይቅ፣ አትመራመር፣ አባቶች ወይም የሃይማኖት መሪዎች ያሉት ትክክል ስለሆነ እንዲሁ ሳትጠይቁና ሳትመረምሩ ተቀበሉ›› ዓይነት የሚመስል አስተምህሮ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ታዲያ  እዚያ በሃይማኖት ቤቶች ቅጥር ግቢ ብቻ የሚቀር ቢሆን መልካም በሆነ ነበር፡፡ ግን የዕለት ዕለት ኑሮአችን ውስጥ የምንከተለው መርህ የሆነ ይመስላል፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ለብዙ ዘመናት ስንጠቀምበት የነበሩ ዕቃዎች እስከ ዛሬ ድረስ ምንም ሳንለውጣቸው እንደነበሩ ያቆየናቸው፡፡ ለምሳሌ የእርሻ መሣሪያዎች ለስንት ሺህ ዘመናት የተጠቀምንባቸው ቢሆኑም ዛሬ ድረስ ለማሻሻልና አዳዲስ ዲዛይኖችን የመጠቀም ባህል ሊዳብር አልተቻለም፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገራችን የገቡ ቴክኖሎጂ ውጤቶችም ቢሆኑ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ እንደሆነ በታሪክ ተመዝቧል፡፡ በተለይ አጼ ምኒልክ ያስገቡአቸው ቴክኖሎጂዎች ብዙ ሲሆኑ የተጋፈጣቸው ውግዘቶችም እንደዚሁ ይበዛሉ፡፡ አዲስ ነገር ሲመጣ፣ ባህል የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚያስቀይር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ታዲያ ቴክኖሎጂዎችን በመቃወም በግንባር ቀደምትነት የሚሳተፉት ካህናት መሆናቸው ስንመለከት ሃይማኖትን የተረዳንበት መንገድ መመርመር እንዳለበት ለማሰብ እንገደዳለን፡፡

የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ የኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም በሚለው መጽሐፉ፡-

“… በሰሜኑ የክርስቲያን ክልል ዘመናዊ ትምህርትና የከተማ ሥርዓት እንዳያድግና እንዳይስፋፋ አንድ ሥርዓታዊ እንቅፋት ሆነ”[1]

ብሎ ጽፏል፡፡ በተለይ በከፍተኛ ደሞዝ ከግብጽ ሲመጡ የነበሩ የግብጽ አቡኖች፦

“ዘመናዊ ትምህርትና የለውጥ ሀሳቦችን፣ የሃይማኖት ትምህርትና ነፃነትን፣ የሚሲዮናውያንን ትምህርትና እምነትን በሚመለከት ጉዳዮች ላይ ሁሉም በነበራቸው ተጻራሪ አመለካከትና አቋም ለአገሪቱ ብሔራዊ አንድነት፣ ለህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ እኩልነትና ማህበራዊ ዕድገት አንድ ታላቅ እንቅፋት ሆኑ፡፡“[2]

ዛሬ በዚህ ዘመን የምናየው የግብጾች ተንኰል ድሮም የነበረ ነው።

ሌላው ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” ብሎ ባሳተመው መጽሐፍ ቄሳውስት ከውጭ አገር ስለሚገቡ ቴክኖሎጂዎች ያላቸው አመለካከት ምን እንደነበረ ማንበብ ይቻላል፡፡ በምኒልክ ዘመን የገቡ ትምህርት፣ ባቡር፣ ስልክ፣ ፖስታ፣ ኤሌክትሪክ፣ አውቶሞቢል፣ ሆቴል…. ወዘተ ሁሉ በቄሳውስት ዘንድ ከፈተኛ ተቃውሞ አስነስተውባቸዋል፡፡ ሃይማኖትና ባህልን እንደሚያጠፋ አድርገው ይከሷቸዋል፡፡ የንጉሱን የመጨረሻ ምረት የምትገልጽ አንዲት ሐሳብ ብቻ ልጥቀስ፡-

ከቀሳውስት የተውጣጡ ስምንት ተወካዮች ከአጤ ምኒልክ ዘንድ ቀርበው ‘ይህ ስልክ የጋኔን ሥራ ስለሆነ ከቤተ መንግስቱ እንዲወጣ፣ ከአገሪቱም ጨርሶ እንዲጠፋ’ ብለው አመለከቱ፡፡ ምኒልክም አሳባቸሁ ደህና ነው፡፡ መልሱን ግን ነገ እነግራችኋለሁ ብለው ካሰናበቱአቸው በኋላ በማግሥቱ መኳንንቱን ሰብስበው ጳጳሱ ባሉበት እነዚሀ ቄሶች በማይሆነው ሁሉ እየተቃወሙ አስቸግረውኛል፡፡ አሁን ደግሞ ስልክ ባገሬ ባስገባ የሰይጣን ሥራ ስለሆነ አስወጣ አሉኝ፡፡ የሰይጣን ሥራ ያለመሆኑንም ነገርኳቸው፡፡ እነሱ ግን በቁማቸው ይቃዣሉ፡፡ ሥራዬንም የሚያደናቅፉኝ ይሆናሉና ከእንግዲህ ወዲያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖቴን ትቼ ከነሱ ለመለየት ስል ሃይማኖቴን መለወጤ ነው አሉ[3]፡፡ 

ይህ በወቅቱ ንጉሱ ምን ያህል እንደተቸገሩ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ ጉዳይ ከአንድ ቤት ክርስቲያን ጋር የተያያዘ ቢመስልም ነገሮችን ከሰይጣንና ከእግዚአብሔር ጋር ማገናኘት አጠቃላይ የአገሪቱ ባህል ይመስላል፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ

“በብዙ የቅዱሳንና የአጋንንት እርዳታ እንደ ኢትዮጵያችን ነገስታትና ገዦች የሚያስፈልገው ሰው በዓለም ታሪክ ከቶ አልተሰማም”[4]

ብለው የፃፉት፡፡

ለ. የሰውን ሚና ማሳነስ

ሌላው ሐሳብ በፈጣሪ ላይ ያለን የመደገፍ መጠን ኃላፊነታችንን እንድንዘነጋ ያደረገን ይመስለኛል፡፡ እዚህ ጋር የፕሮፌሰር መስፍንን ግምገማ ላስቀምጥ፡፡

“ኢትዮጵያ ሕዝብ ለክፉውም ሆነ ለደጉ፣ ለሐዘኑም ሆነ ለደስታው ኃላፊነቱ በሙሉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የራሱ እንዳልሆነ አድርጎ የሚመለከተው ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ነገር ሕዝቡ ችግሩን ለመድሃኔ ዓለም፣ ለአማኑኤል፣ ለኢየሱስ፣ ለአላሕ፣ ለማሪያም፣ ለኪዳነ ምህረት፣ ለገብርኤል፣ ለሚካኤል፣ ለአቦ፣ ለተክለ ሃይማኖት፣… ወዘተ አስተላለፍፎ እነሱ እንደችሮታቸው ያድርጉት ብሎ ይጠብቃል፡፡ በዚህ መልኩ ጸሎት ማለት ኃላፊነትን ማውረድ ማለት ነው[5]፡፡

በፈጣሪ ላይ መደገፍ በአምላክ (አማልክት) በሚያምኑ ሃይማኖቶች ሁሉ የሚበረታታ ቢሆንም የሰው ልጅ በራሱ የሚወጣው ኃላፊነት እንዳለ ደግሞ መገንዘብ ያሻል፡፡ የደረሱብን ችግሮች ምናልባት በራሳችን ድክመት ምክንያት አሊያም በሌሎች ሰዎች ክፋት እንጂ የአርባ ቀን ዕድላችን እንዳልሆነ ስንገነዘብ ለለውጥ እንነሳሳለን፡፡ ፈጣሪ ችግሮቻችንን እንድናሸንፋቸው አቅም ይሰጠናል እንጂ እሱ ራሱ ወርዶ በተዐምራት አያሰወገድልንም፡፡

የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር እንዲታገል የተፈረደበት ፍጡር ነው፦

“ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።[6]

የተባለው የመጽሐፉ ቃል ለመላው ዓለም የሚሠራ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሮቻችን ፈጣሪ በሰጠን አቅም እንድንታገላቸው እንጂ ፈጣሪ ያመጣብን ቅጣት ነው በማለት አሊያም በልፋት የሚወገደውን በጸሎት ብቻ እንዳንሞክረው ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ጸሎት የሰንፍናችን መሸፈኛ ካባ መሆን የለበትም።

አነስተኛ ደመወዝ

አገራችን ድሃ እንደመሆኗ መጠን ዜጎች የሚለፉትን ያህል ስለማይከፈላቸው ትጋታቸው እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆነኝ ውጪ አገር የሚኖሩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውን ናቸው፡፡ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ማንኛውም የዓለም ማኅበረሰብ በትጋት የሚሠሩ እንደሆነ እንሰማለን፡፡ እንደ ሠለጠነው ማኅበረሰብም ሥራ ሳይንቅ የተገኘውን ሁሉ እየሠራ እንደሚኖር እናውቃን፡፡ የዚህ ምስጢር ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ የለፉትን ያህል ስለሚያገኙ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥም ሰዎች የለፉትን ያህል ቢከፈላቸው እንደ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ ተግቶ የማይሠራበት ምክንያት ምንድን ነው?

ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ባህል ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ የደሞዝ አከፋፈላችን ሁኔታ መጤን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደምናውቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ከወር እስከ ወር እያንዳንዷን ደቂቃ በሥራ ሲባትሉ የሚሠሩና ምንም ዓይነት ሥራ ሳይነኩ ከቤት ወደ መ/ቤት ከመ/ቤት ወደ ቤት ሰርክ የሚመላለሱ ሰዎች በወሩ መጨረሻ እኩል ደሞዝ ማግኘታቸው ነው፡፡ የሚተጋውም የሚለግመውም እኩል ደሞዛቸውን ያገኛሉ፡፡ በተለይ ይህ አባዜ በመንግሥት መ/ቤቶች ውስጥ የተንሰራፋ ባህል ነው፡፡ ክፋቱ ደግሞ አንዳንዴ ብዙ ሥራ የማይወዱ ሰዎች ለአለቆቻቸው ስለሚያጎበድዱ ብቻ ጥቅማ ጥቅሞችና የሥራ ላይ ዕድገት (Promotion) በሚመጣበት ጊዜ ቀዳሚ ተጠቃሚዎች የሚሆኑበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ይህ የሚሠራውን ሰው ሞራል የሚገድል አደገኛ ልማድ ነው፡፡

ስለዚህ ሥራ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ አንደኛ የደሞዝ አከፋፈል ሥርዓታችንን እንደገና መፈተሸ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ከወራዊ ደሞዝ ይልቅ ሰዎች በሠሩት ሰዓት ልክ ቢከፈላቸው የሚተኛ አይኖርም፣ የተሻለ ለማግኘት ብቸኛ አማራጭ ብዙ ሰዓት ወደመሥራት ይለወጣል፡፡ ደሞዝ ለሁሉም ሰው የሚገባ የመብት ጥያቄ ሳይሆን ስለ ሠሩ ብቻ የሚሰጥ የልፋት ዋጋ ነው።

አቴንዳንስ ተኮር የሥራ ባህል

ብዙውን ጊዜ ‹ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በቀን 8 ሰዓት መሥራት አለበት› ይባላል፡፡ ይህ የሚያሳየው ሰዎች በተቀጠሩበት መ/ቤት የሚቆዩት ለስምንት ሰዓታት ያህል ብቻ ነው፡፡ አለቆቻቸውም ሰዎች ምን ያህል ተግባራት አከናወኑ የሚለውን ሳይሆን የቆዩበትን ሰዓት ብቻ ያሰላሉ፡፡ ይህ አካሄድ በአካል ተገኝተው አንዳችም ነገር ሳይሠሩ የሚመላለሱ ሠራተኞችን የፈጠረ ይመስላለ፡፡ ሲገቡ ይፈርማሉ፣ የለም እንዳይባሉ አሉ፡፡ ምን ምን ሠሩ ሲባል ግን አጠያያቂ ይሆናል፣ የወር ደሞዛቸውን የሚነካ ግን የለም፡፡

አቴንዳንስን መሠረት ያደረገ የሥራ ባህላችን መቀየር አንዱ መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያ ማለት አቴንዳንስ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ከአቴንዳንስ ባሻገር ለሁሉም ሠራተኛ ሥራ ቆጥሮ መስጠትና ውጤቱን ቆጥሮ መቀበል የተሻለ አቀራረብ ነው፡፡ ግልጽ የሆነ ዕቅድ ካለ፣ ዕቅዱን ወደ ሩብ ዓመት፤ ከሩብ ዓመት ወደ ወራት፣ ከወራት ወደ ሳምንታት፤ ከዚያም ወደ ቀናት መሸንሸን ይቻላል፡፡ ከዚያም ለሁሉም ሠራተኛ የድርሻውን ማከፋፈል፡፡ ሠራተኞቹ በየቀኑ የደረሳቸውን ድርሻ ከቻሉ በአንድ ሰዓት ከቻሉ በ8 ሰዓት ይጨርሱ፡፡ ኃላፊው ሠራተኛው ገባ አልገባ እያለ አቴንዳንስ ላይ ፊርማ መቁጠር ሳይሆን ያከፋፈለው ተግባር ማብቂያ ሰዓቱ ሲደርስ ከሁሉም ሠራተኛ ውጤቱን እየሰበሰበ ይገመግመዋል ማለት ነው፡፡ ያኔ ማን የተሰጠውን ኃላፊነት በጊዜ እንደሚያስረክብና እንደማያስረክብ መለየት ይችላል፡፡ በዚህም ጎበዝና ልግመኛ ሠራተኛን ይለያል፡፡ ጎበዞችን በመሸለምና ልግመኞችን በመቅጣት ወይም አቅም እንዲያሳድግ ተጨማሪ ሥልጠና በመስጠት ውጤታማ የሥራ ባህል መፍጠር ይቻላል፡፡ ሠራተኛም ‹‹አለቃ አየኝ አላየኝ›› ዓይነት የድብብቆሽ ጫወታ ከመጫወት ወይም አቴንዳንስ ብቻ ፈርሞ እዚህም እዚያም ሲንገላወድ ከመዋል ወጥቶ ሥራውን አለቃ አድርጉ ተግቶ ይሠራል፡፡

አንዳንዴ ግን ችግር የሚኖረው አሠሪዎች (ኃላፊዎች) ጋር ነው፡፡ ሠራተኞቻቸው ምን እንዲሠሩላቸው በወጉ ያላወቁ ኃላፊዎች ቀይ እስክርቢቶ ይዘው አቴንዳንስ ጋር ቁጭ ብለው ይውላሉ፡፡ ሠራተኛው የተሰጠው ኃላፊነት በሥርዓት ሠርቶ ድንገት አቴንዳንስ ባይፈርም ሥራ እንዳልሠራ ይቆጠራሉ፡፡ ይኸ ፈተና ይሚደርሰው ብዙውን ጊዜ ከአቴንዳንስ በላይ ሥራቸውን የሚያከብሩና ትኩረቱን ሥራ ላይ ብቻ የሚያደርጉ ትጒህ ሰራተኞች ላይ ነው፡፡ ሥራውን ሠርተውታል፣ ግን አቴንዳንስ አልፈረሙም፡፡ ኃላፊዎቻቸው ሥራውን ሳይሆን አቴንዳንስን እንደ ሥራ ስለሚቆጥሩ ‹እንዳልሠሩ› ይቆጥሯቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሰውዬ ተስፋ ቆርጦ ‹‹ዋናው አቴንዳንስ ከሆነ እዲያውም ፊርማ መፈረም ቀላል ነው›› ይልና ከታታሪ ሠራተኝነት ወደ ፊርማ ፈራሚነት ይወርዳል፡፡ አቴንዳንስ ሥራ አይደለም፣ ሰው አታላይና አጭበርባሪ ባይሆን አቴንዳንስ አያስፈልግም ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሰው ልጆች ተንኮል አቴንዳንስ የግድ እንደፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡

ሥራ የማጣት ስጋት አለመኖር

በተለይ በመንግሥት መ/ቤቶች የተቀጠሩ ሰዎች ሥራ የማጣት ስጋት የለባቸውም፣ ቢኖርም በጣም አልፎ አልፎ ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ግድፈት ካልፈጠረ በስተቀር የተሰጠውን ኃላፊነት በትክክል ባለመወጣቱ ምክንያት የተባረረ ሰው አይተንም ሰምተንም አናውቅም፡፡ ይህንን ለመረዳት በግል ተቋማትና በመንግሥት መ/ቤቶች የሚሠሩ ሰራተኞችን ማወዳደር ነው፡፡ በእኔ ግምገማ በግል ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሠሩ ሰራተኞች የበለጠ ይታትራሉ፡፡ ለምን ቢባል የግል ድርጅቶች ለትርፍ የተቋቋሙ ስለሆኑ ሰራተኞቻቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ውጤታማ መሆን ካልቻሉ ሥራቸውን የማጣት አደጋ ያንዣብብባቸዋል፡፡ በግል ድርጅቶች ውል ማቋረጥ ቀላል ነው፣ በመንግሥት መ/ቤቶች ግን ሂደቱ ብዙ ነው፡፡

ሰዎች በተፈጥሮ በጃቸው ያለ ነገር እንደማያጡት ከተረዱ ዋጋ ያሳጡታል፡፡ አየር ርካሽ የሚመስለን ብዙውን ጊዜ ስለማናጣው ነው (ያጣን ዕለት ግን ያለ እሱ ለደቂቃዎች መቆየት እንደማንችል እንገነዘባለን) ፡፡ ለመኖር የምንታገለው ሞት ስላለ ነው፣ ጤንነትን የምንወደው መታመም ስላለ ነው፣ ለሰላም ዋጋ የምንከፍለው ጦርነት (ጥል) አስከፊ ስለሆነ ነው፡፡ ያገኘነውን አጥብቀን የምንይዘው ማጣት ስላለ ነው፡፡ የማጣት ስጋት ትግል ያመጣል፣ ትግል ወደ የተሻለ ውጤት ያስጠጋል፡፡ ነገር ግን መ/ቤቶቸ ያለው ሁኔታ ስንመለከት ሰዎች እንደምንም ብለው እግራቸውን ያስገቡ እንጂ አንዴ ቋሚ ሠራተኛ ሆነው ከተቀጠሩ የሚነካቸው የለም፡፡ሥራ የማጣት ስጋት የለባቸውም፡፡ ከዚህ የተነሣ ሥራቸውን ላለማጣት ብለው አይታገሉም፡፡ 

ጊዜውን የሚመጥን የክህሎት ለውጥ አለመያዝ

በአገራችን አንዱና ዋንኛው ችግር በምንማረውና በምንሠራው መካከል ሰፊ ክፍተት (Gap) መኖሩ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ችግሮ እንደ ችግር ታይቶ መፍትሄ ለማምጣት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል እንጂ ከዚህ በፊት የምናውቀው አብዘኛው ሠራተኛ ከተማረበት ሙያ ውጪ ሲሠራ ኖሯል፡፡ እንደሚታወቀው ትምህርት የምንማረው የተሻለ ክፊያ ለማግኘት እንጂ የውስጣችንን ዝንባሌና ፍላጎት (Passion) የተከተለ ስላልሆነ ከተማርንበት ሙያችን ውጪ የተሻለ ክፊያ የሚገኝበት የሥራ መስክ ለመቀየር አናመኔታም፡፡ ይህ በሥራ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ የተፈጠሮ ሳይንስ ተማሪ የሆነ ሰው አንድ መ/ቤት እንዲያስተዳደር ኃላፊነት ቢሰጠው በምን አቅሙ ሊያስተዳድር ይችላል? ምክንያቱም ሰውን ማስተዳደር ራሱን የቻለ ሙያ ስለሆነ፡፡

ይህ ማለት ግን ሰዎች ከሙያቸው ውጪ አይውጡ ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም ነገር ዕውቀት እንደሚጠይቅ አውቀው ያለባቸውን ክፈተት ለመሙላት የበለጠ ሊሠሩ ይገባል፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ከተመረቁ በኋላ ሙያቸውን ሳያሳድጉ ለረጅም ዘመናት አንድ ቦታ ላይ ይከርማሉ፡፡ ተቀያያሪ በሆነ ዓለም የሚኖር በየጊዜው ከሚቀያየረው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እራሱን ካልቀየረ በአንድ ቦታ ላይ ተቸንክሮ መቅረትን ያመጣል፡፡ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሙያቸውን ለማሳደግ ብዙ ብር ከፍለው እንኳን አጫጭር ሥልጠናዎችን ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡ በየዞንና ወረዳ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ግን ይህንን የሚያገኝበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ከኮሌጆች ወይም ከዩኒቨርሲቲዎች ከተመረቁ በኋላ ሙያቸውን የሚያሳድጉበት ምንም ተጨማሪ ሥልጠና ሳይወስዱ ለዘመናት የሚከርሙ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ይህም በሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡

የሚገኙ የሥልጠና ዕድሎችም ከአበል አንጻር ብቻ ማየት ደግሞ ሌላ ፈተና ነው፡፡ የማውቀውን አንድ ታሪክ እዚህ ጋ ላስታውስ፡፡ ከተቋሙ አዲስነት የተነሣ ቴክኒክና ሙያ ላይ የሚያስተምሩ መምህራን ብዙውን ጊዜ የክሎት ክፍተት አለባቸው ተብሎ ስለሚታመን ክረምት ላይ የክህሎት ክፍተት ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረግ ነበር፣ በተለይ የመንግሥት ተቋማት ላይ ለሚሠሩ፡፡ እኔም ባንድ ወቅት ላይ በእንደዚህ ዓይነት ሥልጠና ላይ የመሳተፍ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ሥልጠናው ለ 2 ወራት የሚቆይ ነበር፡፡ በዚያ ሥልጠና ላይ የተገነዘብኩት ነገር ብዙ መምህራን መሠረታዊ የክህሎት ክፍተት እንዳለባቸው ነው፡፡ ስለዚህ ሥልጠናው አስፈላጊ ነበር፡፡ ሆኖም ግን መምህራኑ ሥልጠናውን ሳይሆን በሥልጠናው ሰበብ የምትሰጠውን አበል ብቻ እንደሆነ ተገነዘብኩ፡፡ ‹‹አበላችንን ሰጥተው ለምን አይሸኙንም? ›› የሚሉ ጩኸቶች በርክተዋል፡፡ ለ2 ወራት የተባለ ሥልጠና በብዙ ግብ ግብ ለ1 ወር ያህል ብቻ ተሰጥቶ አለቀ፡፡

ዕውቀት የምንፈልግ አይመስለኝም፤ በወርቀት ብቻ የሚያምን ባህል ያዳበርን ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የተነሣ ትላልቅ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እንኳን ተመድበን ያንን ቦታ የሚመጥን የመሪነት አቅም ለመገንባት ጥረት ስናደርግ የማንታየው፡፡ ሙያችንን ለማሳደግ ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ አንዱ አጫጭር ሥልጠናዎችን በመውሰድ ነው፡፡ ሌላው ማንበብ ነው፡፡ በእርግጥ ለየትኛውም ሥራ ማንበብ ፍቱን መድኀኒት ነበር፡፡ ማንበብ የግድ ከሥራችን ጋር የተያያዘ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ማንበብ አስተሳሰብን ስለሚገራ ወሳኝ ተግባር ነበር፡፡ የተማረ ሰው ሆኖ ማንበብ የሚጠላ ሰው ማግኘት እንዴት ያሳዝናል፡፡ በተለይ መሪ የሆነ ሰው ማንበብ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡


[1] ላጵሶ ጌ.ድሌቦ(ዶር)፣ የኢትዮያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም 1900-1966 (1983) አ.አ ገጽ. 99

[2] ዝኒ ከማሁ ገጽ. 103

[3] ጳውሎስ ኞኞ፣ አጠ ምኒልክ (1984) ገጽ. 259

[4] ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች (2007 ዓ.ም) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕረስ ገጽ 5

[5] መስፍን ወልደ ማሪያም፣ ኢትዮጵያ ከየት ወደት (1986 ዓ.ም) ጉራማይሌ አሳታሚ አዲስ አበባ

[6] ኦርተ ዘፍጥረት 3፡19