የኢትዮጵያ የሥራ ባህል

የኢትዮጵያ የሥራ ባህል

ሥራ ምንድን ነው?

ሥራ ስንል ምን ማለታችን ነው? ጧት ከእንቅልፉ ተነሥቶ ቦርሳውን አንጠልጥሎ የመንግሥት መ/ቤት የሚሄድና ቤት ውስጥ ቀርቶ ምግብ የሚያበስል፣ ልብስ የሚያጥብ ወይም ልጆችን የሚንከባከብ ሰው እኩል ሥራ ሠርተዋል እንላለን? ሥራን ሥራ የሚያስብለው ደሞዝ ስለማስገኙቱ ነው ወይስ ሌላ ጥቅም ስላለው ነው? እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን መጠየቅ በአገራችን ብዙ የተለመዱ ባይሆንም በተግባር ግን የምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ ለምሳሌ ቤት ውስጥ በባልና ሚስት መካከል ግጭት ከሚያስከትሉ አጀንዳዎች መካከል የአንዱ የትዳር አጋር ተቀጣሪ ሠራተኛ መሆንና ሌላኛው በቤት ውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ብቻ መወሰን ነው፡፡ ተቀጥሮ ደሞዝ የሚያገኘ ሰው ሥራ አለው ይባላል፣ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ሰው ብዙ ሥራ ቢሠራም ሥራው ደሞዝ ስላላስገኘለት ብቻ እንደ ሥራ አይቆጠርም፣ ባለቤቱም ሥራ ሠርቻለሁ ብሎ አያምንም፡፡ ይህ አመለካከት ሥራ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ተግባራትን ማከናወን እንደሆነ ታሳቢ የሚያደርግ ነው።

አንድ ገጠመኝ እዚህ ጋር ብጠቅስ ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከኔ ጋር አንድ ግቢ ተከራይተው የሚኖሩ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ባል ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ላይ ነው የተሰማራው፡፡ ሚስት በበኩሏ ተቀጣሪ አልነበረችም፡ ገቢ የሚያስገኝ ሥራም የላትም፡፡ ባል የሚያገኘው ገቢ ለኑሮአቸው በቂ ስለነበረ ስለሚበሉትና ስለሚለብሱት ነገር ብዙ አይጨነቁም፡፡ ሆኖም ግን ሚስተዬው በሕይወቷ ደስተኛ አልነበረችም፡፡ እሱ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ስትነጫነጭ አያታለሁ፡፡ አንድ ቀን ጠየቅኳት፡፡ እሷም እንደ ሰው ጧት ለሥራ የምትወጣበት ቀን እንደ ናፈቃት አጫወተችኝ፣ እኛ ሥራ ስንወጣ እሷ ከልጆቿ ጋር ቤት ውስጥ ስለምትውል ሰለቻት፡፡ ‹‹እስከ መቼ ነው የቤት እመቤት ሆኜ የምኖረው? ›› አለችኝ፡፡ በቂ መልስ አልነበረኝም፣ በኔ እምነት ሥራ እየሠራች እንደሆነ ነው የማውቀው፡፡ እንዲያውም ከማናችን በላይ ብዙ ሥራ የምትሠራው እሷ ነበረች፡፡ ጧት ገና ከእንቅልፋችን ሳንነሣ ተነስታ ት/ቤት ለሚሄደው ልጇና ሥራ ለሚሄደው ባሏ ቁርስ ትሠራለች፣ ልጇን ት/ቤት ትወስዳለች፣ እንደገና ተመልሳ ምሳ ትሠራለች፣ ልብስ ታጥባለች… ቀን ሙሉ ግቢ ውስጥ ስትንቀሳቀስ ነው የምትውለው፡፡ ባሏም በሥራ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ቤት ስለማይኖር የማስተዳደር መሉ ኀላፊነት ተረክባ ቤቱን ትመራለች፤ ያ ሁሉ ብታደርግም ቅሉ አእምሮዋ ሥራ እየሠራች እንዳልሆነ ይነግራታል፡፡ በዚህም ትከፋለች፡፡ ከዚያ በኋላ ስለ ሥራ አንድ ነገር ተረዳሁ፡፡ ሥራ ደሞዝ የማገኘት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ቢያንስ ለአእምሮ እረፍት ሥራ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ይህች ሴት ብር አልጎደላትም፣ ሥራ የምትፈልገው ገቢ ለመጨመር ብላ አይደለም (እሱን ማሰብ ባይቀርም)፣ ዋና ፍላጎቷ ከሰዎች ጋር እኩል ሆና መታየት ነው፣ ወጥቶ መግባት፡፡ እንቲና እኮ ሥራ አላት ለመባል። ቤት ውስጥ የፈለገውን ያህል ጉልበት አውጥታ ብትደክም አእምሮዋ ‹ሥራ የለሽም› ይላታል፡፡ ምንም እንኳን ባሏ የእሷ ሥራ እጅግ በጣም ወሳኝና ለሱ ሥራም ጭምር መሠረት እንደሆነ ብነግራትም አእምሮዋ ግን አይቀበልም፡፡ ይህ የብዙ ሰዎች ችግር ይመስለኛል።

በተለይ ይህ እሳቤ በከተሞች አካባቢ ጫናው የሚበረታ ይመስለኛል፡፡ ገጠር አካባቢ ያለው ሥራ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ከመሆኑም ባሻገር ሁሉም የቤተሰብ አባል አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያዋጣል፡፡ ሥራ የሚለካው ገንዘብ ወይም አንዳች ገቢ በማስገኘቱ ሳይሆን ቤተሰቡ ከሚያከናውናቸው ዕለታዊ ክንውኖች መካከል አንዱ መሆኑ ብቻ በቂ ነው፡፡ ልጆች ከብት ይጠብቃሉ፣ ውኃ ይቀዳሉ፣ እንጨት ይለቅማሉ፡፡ እናቶች ቤት ውስጥ ሆነው ምግብ ያበስላሉ፣ ቤት ያጸዳሉ፣ ለባሎቻቸው ስንቅ ያደርሳሉ፣ አንዳንዴም ከባል ጋር እርሻ ላይ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በመተጋገዝ ላይ የተመሠረተ ሕይወት ይመራሉ፡፡

የከተማ ሕይወት ግን ከዚህ የተለየ ፈርጅ አለው፡፡ በተለምዶ “ሥራ” ተብሎ የሚታሰበው ቀጥታ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ተቀጥሮ መሥራት ይፈልጋል፡፡ በተለይ የካፒታሊዝም አስተሳሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ማንኛውም ዓይነት ሥራ ከገቢ አንጻር እንዲመዘን አድርጎታል፡፡

የሥራ ትርጉም

ሥራ እንደየአውዱ የተለያዩ ትርጉሞችን ሊይዝ ይችላል፡፡ ቤት ውስጥ ምግብ የሚያበስል ሰው ‹‹ሥራ እየሠራሁ ነው›› ሊል ይችላል፡፡ የመንግሥት (መንግሥትም ያልሆነ) መ/ቤት የሚሄድ ሰው ‹‹ሥራ እየሄድኩ ነው›› ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ሥራ ማንኛውም አካላዊም ሆነ አእምሮአው ድርጊቶችን ለመወከል የሚውል ቃል መሆኑን ነው፡፡

በእንግሊዝኛ Work የሚለው ቃል ከዚህ በላይ ያየነው ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሥራ ሁሉንም እንቅስቃሴ ያቀፈ ነው፡፡ በሌላ ጎን ግን Job የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ከሥራ ትንሽ ጠበብ ያለ መልዕክት አለው፡፡ አንድ ሰው ‹‹ሥራ ይዟል›› ከተባለ በአንድ መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ባልሆነ ተቋም ውስጥ ተቀጥሯል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያ ሰው ሥራ አለው እንላለን፡፡ ሆኖም ግን ያ ሰው ‹‹ሥራ አለው›› ማለት ብቻ በቂ መረጃ አይሰጥም፡፡ ምን መደብ ላይ እንደተቀጠረ ወይም እዚያ ድርጅት ውስጥ ምን እንደሚሠራ አልታወቀም፡፡ ይህ Job ወደሚለው ሐሳብ ይመራናል፡፡ Job በዋናነት ሰውዬ የሚያከናውነው ተግባር ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የሒሳብ ባለሙያ፣ አስተማሪ፣ ሐኪም፣ ኃላፊ… ወዘተ

የሥራ ሥነ-ምግባር ምንድን ነው?

የሥራ ሥነ-ምግባር ላይ ውይይት ከማድረጋችን በፊት ሥነ-ምግባር የምንለው ጽንሰ ሐሳብ መረዳት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሥነ-ምግባር ምንድን ነው?

ሥነ-ምግባር በሃይማኖት ወይም በፍልስፍና የሚጠና ሰፊ ሐሳብ ነው። በእንግሊዝኛ “Ethics” እና  “Morality” ሥነ-ምግባርና ግብረ-ግብ ተብለው በአማርኛ የተተረጎሙ ሲሆን ተመሳሳይ ሐሳብን ለመግለጽ ሥራ ላይ ይውላሉ። ሁለቱም ወግ ወይም ልማድ፣ ወይም ጠባይ የሚሉ ትርጉሞችን ይይዛል። ሥነ-ምግባር የሰው ልጆችን ወግ፣ ልማድና ጠባይ የሚመርምርና የሚያጠና የጥናት መስክ በመሆን ያገለግላል። በሌላ በኩል የአንድን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ፣ ትክክል ወይም ስህተት፣ ፍትሐዊ ወይም ኢ-ፍትሐዊ ወዘተ… ብሎ የሚዳኝ ጥናት ግብረ-ገብ (Moral Philosophy) ተብሎ ይጠራል።

ሥነ-ምግባር ማለት በሥርዓት በተደራጀ መለኪያ (Standard) መሠረት ትክክልና ትክክል ባልሆኑ ድርጊቶች መካከል የሚዳኝ፣ በተለይ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው፣ ግዴታዎችን የሚጭን፣ መብትን የሚያጎናጽፍ፣ ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታን የሚያበረታታ የጥናት ዘርፍ ነው[1]፡፡ ሥነ-ምግባር ጤናማ ማኅበራዊ መስተጋብር ለመከወን እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅቡልነት ያላቸው ድርጊቶችንና የተከለከሉትን እንድንረዳ የሚያደርገን እሴት ነው፡፡ የሰው ልጅ የባህሪይ ቀረጻ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው፡፡

የሥራ ሥነ-ምግባር

የሥራ ሥነ-ምግባር ስናወራ ከላይ ካየነው የሥነ-ምግባር እሳቤ ጋር አብሮ የሚጋመድ ነው፡፡ ሥራ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብንና ምን ማድረግ እንደሌለብን የሚያሳይ ሐሳብ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሥራ የራሱ የሆኑ የሙያዊ-ሥነ-ምግባሮች (Professional Ethics) ይኖሩታል:: ከዚህ በተጨማሪ ቀጣሪ ድርጅት ከሠራተኞቹ የሚጠብቀው ድርጊት ይኖራል፡፡ ስለዚህ ቀጣሪ ድርጅቶች ከሠራተኞቹ የሚጠብቁት ጤናማ የሥራ ውጤት ሲደመር ሙያዊ ሥነ-ምግባር የሥራ ሥነ-ምግባርን ይፈጥራሉ፡፡ ለምሣሌ የመንግሥት ሠራተኛ ከሆንን በቁጥር አንድ ከሠራተኞች የሚጠበቀው ነገር በሰዓት መግባትና መውጣት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ በሰዓት ገብቶ በሰዓት እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡ አርፍዶ የሚመጣና ቀድሞ የሚወጣ የሥራ-ሥነ-ምግባሩን ጥሷል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሥራውን በሚያከወናውንበት ጊዜ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር የመላበስ ግዴታ አለበት፡፡ ለምሣሌ፣ የደንበኞችን ምስጢር መጠበቅ፣ በትኅትና ማስተናገድ፣ ጒቦ አለመቀበል ወዘተ… ሙያዊ ሥነ-ምግባሮች ናቸው፡፡ 

በተለምዶ የሥነ ምግባር መርሆች ተብለው በየቦታ የሚጠቀሱ ሐሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡-

 • ቅንነት (Integrity)
 • ታማኝነት (Loyalty)
 • ግልፀኝነት (Transparency)
 • ተጠያቂነት (Accountability)
 • ሀቀኝነት (Honesty)
 • ምስጢር መጠበቅ (Confidentiality)
 • አለማዳላት (Impartiality)
 • ሥልጣን በአግባቡ መጠቀም (Exercise sing Legitimate Authority)
 • ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት (Responsiveness)
 • የሕዝብ ጥቅም ማስቀደም (Sensing The public Interest)
 • ሕግን ማክበር (Respecting the Low)
 • አርኣያ መሆን (Exercising Leadership)

እነዚ ሀሳቦች በየመሥሪያ ቤቶች የተለጠፉ ቢሆንም ምን ያህል ሰው ይተግብራቸዋል የሚለው ግን አጠቀያያቂ ነው፡፡

የሥራ ባህል ምንድን ነው?

ስለ ሥራ ባህል ከማውራታችን በፊት ባህል የሚለው ቃል ትርጉሙን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃለት ‘ባህል’ የሚለውን ቃል የሚፈታው፥-

 “ሀሪሶት፣ የሕብረተሰብ አነጋገር፣ ልማድ፣ እምነት፣ ጠባይ፣ ግበረገብ፣ ዘዴ፣ ሕግ፣ ወግ፣ ብሂል፣ ትውፊት፣ ሥነ ቃል፣ ሥርዓት…. “[2]፡፡

በማለት ነው። ለዚህ ውይይታችን ይረዳን ዘመን ባህልን ለመግለጽ ከተዘረዘሩት ቃላት መካከ ‹‹ልማድ፣ እምነት፣ ወይም ትውፊት›› የሚሉትን መጠቀም እንችላለን፡፡ ባህል ከድግግሞሽ የተነሣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙ ድርጊቶችን፣ እምነቶችን ወይም ትውፊቶችን ያመለክታል፡፡ ስለ ሥራ ስናነሣ የሥራ ባህል የምንለው በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት፣ ልማድ ወይም እምነት እንዴት ያለው ነው የሚለው ሐሳብ ትኩረት ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመርህ ደረጃ የሚታመነውና መሬት ላይ ያለው ሐቅ አንድ ላይሆን ይችላል። ለምሣሌ ማጨስ ጤናን እንደሚጎዳ የማያውቅ ሰው ላይኖር ይችላል፣ ነገር ግን የሚያጨሱ ሰዎች በመርህ ደረጃ እንደሚጎዳ ቢያውቁም በእውኑ ግን አይተገብሩትም፡፡ ስለዚህ ሥራም ስናነሳ እንደዚህ ዓይነት ተፋልሶዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም፡፡ በመርህ ደረጃ ማንም ሥራ መጥፎ ነው ብሎ ላይናገር ይችላል (ሊናገርም ይችላል) ፣ ሆኖም የተናገረውን ላይተገብር ይችላል፡፡

ይቀጥላል. . .


[1] https://www.scu.edu/ethics/ethics-resources/ethical-decision-making/what-is-ethics/

[2] ባህሩ ዘርጋው ግዛው፣ ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ (2010) አዲስ አበባ

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *