የኢትዮጵያ የሥራ ባህል በታሪክ መነጽር ሲቃኝ

የኢትዮጵያ የሥራ ባህል በታሪክ መነጽር ሲቃኝ

ለመሆኑ የሥራ ባህላችን ምን ይመስላል? በተለይ የለውጥ ኃይል የሆነውና ለአንዲት አገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ሠራተኛው እንዴት ነው የሥራ ባህሉ? እስቲ በታሪክ መዛግብት ውስጥ ሥራን በተመለከተ በተበታተነ መልኩ እዚህም እዚያም የተጠቃቀሱ ሐሳቦችን አንድ ላይ ገጣጥመን ሙሉ ሥዕሉን ለማየት እንሞክር፡፡

ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የነበረውና በዘመኑ ታላቅ ምሁር የነበረው ነጋድራሰ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ስለ አገራችን የሥራ ባህል እንዲህ ሲል ይገልጻል፡- 

“የሰውም ክብረቱ ሥራና አእምሮ መሆኑን ገና አላወቅንም ስለዚህ መጽሐፍ የሚያውቀውን ወንድማችንን አስማተኛ፣ ደብተራ፣ የእጅ ሥራ የሚያውቀውን ቡዳ፣ ፋቂም፣ ሸማኔም እያልን እናዋርዳለን[1]”፡፡

ከላይ የሰፈረው ሐሳብ ከመቶ ዓመታት በፊት የተገለጸ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ከመቶ ዓመት በፊት የነበረ ታሪክ ብቻ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፣ ዛሬ ድረስ ሰዎች በሚሠሩት ሥራ ስም እየተሰጣቸው ዝቅና ከፍ የሚደረጉባት አገር እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ወይም ሥራ ሳይሠሩ ደሞዝ መብላት ምንም ቅር የማያሰኘን ሰዎች መሆናችን ዛሬ ድረስ የሥራ ባህል ትንሳኤ አለማግኘቱን ያሳያል፡፡ይህ ሥራ ጠል ባህል ከአገራችን ጋር ረጅም ዕድሜ ያለው መሆኑ ደግሞ ተጽዕኖውን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ይህ ሥራን የመናቅ ታሪክ የተጀመረው ከአክሱም ሥልጣኔ ወደ ላሊበላ ሥልጣነ በተሸጋገርንበት ወቅት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ምክንያታቸው በአክሱም ዘመን ከፍተኛ አክብሮት ሲያስገኙ የነበሩ ሥራዎች ማለትም፦

“የመርከብ ሥራ፣ ብረት የማቅለጥ፣ የሸክላ ሥራ፣ የድልድይ ሥራ፣ የሥነ ሕንፃ፣… የመሳሰሉ የእጅ ሙያዎችና ዕውቀቶች ነበረን፣ ደግሞም መከበሪያዎች ነበሩ[2]  

በዚያ ዘመን ‘ሥራ ክቡር ነው’ የሚባለው አስተሳሰብ ተግባር ላይ የዋለበት ዘመን ነው፡፡ እንደ ዶክተሩ ገለፃ ወደ ላሊበላ ሥልጣኔ ሽግግር ከተደረገ በኋላ ሙያዎቹ መሰደቢያ ወደመሆን ተቀየሩ፤ ደብተራ፣ ቡዳ፣ ፋቂ፣ ቀጥቃጭ፣ አንጥረኛ፣ ቁጢት በጣሽ፣ እየተባለ[3]፡፡

ከላሊበላ ዘመን ጀምሮ ይህ ሥራን የመጥላት አባዜ እንደ ባህል እየተወራረሰ ቀጠለ፡፡ ወደ ኋላ ያለው ታርካችንም ተመሳሳይ ሁኔታ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የኖሩ ዘርዓ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት የተባሉ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች በወቅቱ የነበረውን ማኅበረሰብ ሲመክሩ እንዲህ ብለዋል፡-

የጉልበት ሥራ ለባሮች ነው አትበል፡፡ ቀጥቃጭነትና ግንበኝነትም ለመሳፍንት ልጆች አይገባም አትበል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ በፍላጎቱ (ለሕይወት የሚያስፈልጉት ነገሮች) ሁሉ እኩል ነው፡፡ ይሄ ከመታበይ የሚመጣ ሐሳብ ነው[4]፡፡

እነ ዘርዓ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት ያስተማሩትን ትምህርት ሰምተን ቢሆን ባህሉን የመቀየር ዕድሉ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ምሁራንና ዕውቀታቸውን የመግፋት ባህል ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ትምህርታቸው በተዘጋ ጆሮ ላይ ስለፈሰሰ ሙት የሥራ ባህል ዘመናትን ተሻገሮ ወደ ዘመናዊ ታርካችን ድረስ ዘለቀ፡፡

አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ለማዘመን በተነሱበት ዘመን ሥራን የመጥላት ባህል እንደቀጠለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ንጉሱ “ገበሬ ይረስ፣ ነጋዴ ይነግድ፣ እያንዳንዱ ሰው በየሥራው ይሠማራ” ብለው አዋጅ ያስነገሩት ያንን ሙት የነበረው የሥራ ባህል ላይ ሕይወት ለመዝራት የተደረገ ሙከራ ነበር፡፡ የዚህ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ አንዳንድ ሰዎች የሰጡትን ምላሽ ስናነብ በዚያን ጊዜ አገራችን የነበረችበትን ሁኔታ ያስገነዝበናል፡፡

“ጥቂት ሰዎች ወደ ንጉሱ ግቢ መጥተው፦ <የሀገሪቱ ነዋሪች ሁሉ በሥራ እንዲሠማሩ የሚለውን ንጉሣዊ መመሪያ ለመከተል ይከብደናል> ሲሉ ተናገሩ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በዝርፊያና በቅሚያ ይኖሩ ስለነበር ምንም ሙያ የሌላቸው መሆኑን አስረዱ[5]፡፡

አጼ ቴዎድሮስ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ከሥራ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ አንድ ክስተት እዚህ ጋር ልጨምር፡፡ አንዲት ሴት “ንጉሱ ለሆነች ሴት ሽልማት ሰጠ” የሚል ወሬ ትሰማና በቁንጅና ከተሸላሚዋ ስለምትበልጥ ንጉሱ የሚሸልመው በመልክ ስለመሰላት እሷም በተራዋ ንጉሱ ጋ ትሄዳለች፡፡

ቴዎድሮስ በዚህች ሴት ውበት አልነሆለሉም፣ በምን ቀን ፈጠረሽ ብለው አልተመሰጡባትም፡፡ “ሙያሽ ምንድነው?” አሏት፡፡ እሷም መለሰች ‹‹ሥራ የለኝም የከተማ ቅሬ ነኝ አለች››፤ ቴዎድሮስ ይህች የከተማ ቅሬ- ይህች ገላዋን እየሸጠች ከወንድ በምታገኘው ገንዘብ ራሷን ለማቆንጀት እጅጉን የምትተጋው ይህችን ሴት አዩና፣ “ጥሩ ነዋ! ጥሩ!! እግዚአብሔር ሁለት እጆች የፈጠረልሽ እንድትሠሪባቸው ነበር፡፡ ለመብል ብቻ ከሆነ አንዱ ይበቃሻል!” አሉና አንድ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ “አንድ እጅ ትርፍ ነው፡፡ ካልሠራችበት ምን ያደርግላታል ቁረጡትና ሸኙአት!”[6] 

ትዕዛዙም ተፈጸመ፡፡ ይህንን ድርጊት የታዘበው አንድ አዝማሪ የሚከተለውን ስንኝ ቋጥሮ ለትውልድ አስተላልፏል፡-

ማረስ ይሻላል መገበር፣

እጅ እግርን ይዞ ለመኖር፣

አላርስም ያሉ አልነግድ፣

ተመለመሉ እንደ ግንድ[7]፡፡

ዐጼ ቴዎድሮስ ሥራ ላይ ያላቸው አቋም በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ሥራን ጠልተው በአገልጋይነት ስም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሰከሰኩ ቄሳውስትና ዲያቆናት እጅግ ብዙ ስለነበሩ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ቀርተው ሌሎች በገዛ እጃቸው ሠርተው እንድኖሩ እስከማስገደድ ድረስ ሄደዋል፡፡

አገራችንን ለማዘመን ቆርጠው የተነሱ ነገሥታት ሁሉ ከሚገጥማቸው ፈተናዎች መካከል ሥራን አለመውደድ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የተነሣው አጼ ምኒልክም ይሄ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ንጉሱ ይህንን ክፉ ባህል በአዋጅ እስከማገድ ድረስ ደርሰዋል፡፡ በወቅቱ በሠራተኞ ላይ የሚደርሰውን ስድብ ለማስቀረት የሚከተለውን አዋጅ አስተላልፈዋል: –

ሠራተኛን በሥራው የምትሰድብ ተወኝ።

ከዚህ ቀደም ብረት ቢሠራ ጠይብ፣ ሸማ ቢሠራ ሸማኔ፣ ቢጽፍ ጠንቋይ፣ ቤተ ክርስቲያን ቢያገለግል ደብተራ እያላችሁ፣ አርሶ ነጩን ከጥቊር አምርቶ የሚያገባውን አራሽ ከዘውድ ይበልጣል የሚባለውን ገበሬ እያላችሁ፣ ነጋዴን ነግዶ ወርቊን ግምጃውን ይዞ ቢገባ አንተ ነጋዴ ገባጣ አጣቢ እያላችሁ በየሥራው ሁሉ ትሰድባላችሁ። ልጁ ምናምን ሥራ የማያውቀው ሰነፉ፣ ብልሁን እየተሳደበ አስቸገረ። ቀድሞም ይህ ሁሉ ፍጥረት የተገኘው ከአዳምና ከሔዋን ነው እንጂ ሌላ ሁለተኛ ፍጥረት የለም[8]

በነ ምሊልክ ዘመን የነበሩ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝም ይህንን ሥራ የሚንቅ ባህል ክፉኛ ኲንነውታል፡፡ ሆኖም ግን ነገሮች ከዚያ በኋላም የተለወጡ አይመስልም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ ብዙ ለውጥ የመጣ አይመስልም፡፡ በተለይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች በተመደቡበት ቦታቸው ላይ እንደሚጠበቅባቸው ቢሠሩ ኖሮ ብዙ የተገልጋዮች ሮሮ ባልሰማን ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ከሥራ ይልቅ በሰብሰባ፣ በግምገማና የተለያዩ አገሮችን በመዞር የሚያሳልፉት ጊዜ እጅግ የሚበዛ ሆኖ ይታያል፡፡ አገራችን ከገባችበት የድህነት አዘቅት የሚያወጣት ሥራን የማይጸየፍ፣ በታማኝነትና በኃላፊነት የሚሠራ ትውልድ ሲፈጠርባት ነው።


[1] ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ሥራዎች ገ.20

[2] ብሩህ ዓለምነህ፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና

[3] ብሩህ ዓለምነህ፣

[4] ሐተታ ወልደ ሕይወት፣ ምዕራፍ 18፣ ብሩህ ዓለምነህ የኢትዮጵያ ፍልስፍና በሚለው መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰ

[5] አንደርዜይ ባርትኒስኪና ዮዓና መንቴል-ኒችኮ፤ የኢትዮጵያ ታርክ፣ ከመጀመሪያ እስከ አሁኑ ዘመን፣ ትርጉም በዓለማየሁ አበበ (2005 ዓ.ም)

[6] እንዳለጌታ ከበደ ያልተቀበልናቸው፣ 2009 ዓ.ም ገ. 154

[7] እዚያው

[8] ጳውሎስ ኞኞ፣ አጤ ምኒልክ (1984 ዓ.ም) ገጽ 238